Exodus 11

በበኵሮች ላይ የወረደ መቅሠፍት

1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በፈርዖንና በግብፅ ላይ አንድ ሌላ መቅሠፍት አወርድባቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ፈርዖን ይለቅቃችኋል፤ ሲለቅቃችሁም አንዳችሁን ሳያስቀር ያስወጣችኋል። 2ለእስራኤል ሕዝብ፣ ለወንዶቹም ሆነ ለሴቶቹ የብርና የወርቅ ዕቃዎች ከየጎረቤቶቻቸው ስጡን ብለው እንዲወስዱ ንገራቸው።” 3እግዚአብሔርም (ያህዌ) እስራኤላውያን በግብፃውያን ዘንድ ሞገስ እንዲያገኙ አደረጋቸው። ሙሴም በግብፅ ምድር በፈርዖን ሹማምትና በመላው ሕዝብ ዘንድ እጅግ የተከበረ ሰው ሆነ።

4ከዚህ በኋላ ሙሴ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ ‘እኩለ ሌሊት ሲሆን በመላው የግብፅ ምድር ላይ ዐልፋለሁ። 5በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከፈርዖን ልጅ አንሥቶ የወፍጮ መጅ ገፊ እስከ ሆነችው እስከ ባሪያዪቱ ልጅ ድረስ በግብፅ ምድር በኵር ሆኖ የተወለደ ወንድ ልጅ ሁሉ ይሞታል፤ እንዲሁም የቀንድ ከብቱ በኵር በሙሉ ያልቃል። 6በግብፅ ምድር ሁሉ ከዚህ በፊት ያልተሰማ ወደ ፊትም የማይሰማ ታላቅ ዋይታ ይሆናል። 7በእስራኤላውያን ዘንድ ግን በሰውም ሆነ በእንስሳት ላይ ውሻ እንኳ አይጮኽባቸውም።’ በዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ) በግብፃውያንና በእስራኤላውያን መካከል ልዩነት የሚያደርግ መሆኑን ታውቃላችሁ። 8ሹማምትህ በሙሉ ወደ እኔ ይመጣሉ፤ እጅ እየነሡም ‘አንተም ሆንህ የምትመራቸው ሰዎች በሙሉ ውጡልን’ ብለው ይለምኑኛል፤ እኔም ከዚያ በኋላ እሄዳለሁ።” ከዚያም ሙሴ በታላቅ ቍጣ ከፈርዖን ዘንድ ወጣ።

9 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን “ድንቅ ሥራዎቼ በግብፅ ምድር በብዛት ይታዩ ዘንድ ፈርዖን እናንተን አይሰማችሁም” አለው። 10ሙሴና አሮንም እነዚህን ድንቅ ታምራት በፈርዖን ፊት አደረጉ። ነገር ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ ፈርዖንም እስራኤላውያን ከአገሩ ለቅቀው እንዲሄዱ አልፈቀደም።

Copyright information for AmhNASV